Ecclesiastes 7

ጥበብ

1መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል፤
ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል።
2ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ፣
ወደ ሐዘን ቤት መሄድ ይሻላል፤
ሞት የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፤
ሕያው የሆነም ይህን ልብ ማለት ይገባዋል።
3ሐዘን ከሣቅ ይሻላል፤
ያዘነ ፊት ለልብ መልካም ነውና።
4የጠቢባን ልብ በሐዘን ቤት ነው፤
የሞኞች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው።
5የሞኞችን መዝሙር ከመስማት፣
የጠቢባንን ሰዎች ተግሣጽ መስማት ይሻላል።
6የሰነፎች ሣቅ፣
ከድስት ሥር እንደሚንጣጣ የእሾኽ ማገዶ ነው፤
ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

7ግፍ ጠቢብን ሞኝ ያደርጋል፤
ጕቦም ልብን ያበላሻል።
8የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል፤
ትዕግሥተኛም ከትዕቢተኛ ይሻላል።
9የሞኞች ቍጣ በዕቅፋቸው ውስጥ ስለሆነ፣
በመንፈስህ ለቍጣ አትቸኵል።

10አንተም፣ “ከእነዚህ ቀናት የቀድሞዎቹ ለምን ተሻሉ?” አትበል፤
እንዲህ ያሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ጠቢብነት አይደለምና።

11ጥበብ እንደ ርስት መልካም ነገር ነው፤
ጠቃሚነቱም ፀሓይን ለሚያዩ ሰዎች ነው።
12ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣
ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤
የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣
ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው።
13እግዚአብሔር ያደረገውን ተመልከት፤

እርሱ ያጣመመውን፣
ማን ሊያቃናው ይችላል?
14ጊዜው መልካም ሲሆን፣ ደስ ይበልህ፤
ጊዜው ክፉ ሲሆን ግን ይህን ዐስብ፤
እግዚአብሔር አንዱን እንዳደረገ፣
ሌላውንም አድርጓል፤
ስለዚህ ሰው ስለ ወደ ፊት ሁኔታው፣
ምንም ሊያውቅ አይችልም።
15በዚህ ከንቱ በሆነው ሕይወቴ እነዚህን ሁለቱን ነገሮች አይቻለሁ፤

ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ፣
ኀጥእም በክፋቱ ዕድሜው ሲረዝም።
16እጅግ ጻድቅ፣
እጅግም ጠቢብ አትሁን፤
ራስህን ለምን ታጠፋለህ?
17እጅግ ክፉ አትሁን፤
ሞኝም አትሁን፤
ለምንስ ያለ ቀንህ ትሞታለህ?
18አንዱን ይዞ ሌላውንም አለመልቀቅ መልካም ነው፤
እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው
ጽንፈኝነትን ያስወግዳል
ወይም ሁለቱንም ይከተላቸዋል


19በአንድ ከተማ ካሉ ዐሥር ገዦች ይልቅ፣
ጥበብ ጠቢቡን ሰው ኀያል ታደርገዋለች።

20ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ
ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም።

21የሚነገረውን ቃል ሁሉ ለማዳመጥ አትሞክር፤
አለዚያ አገልጋይህ ሲረግምህ ትሰማ ይሆናል፤
22ብዙ ጊዜ አንተ ራስህ፣
ሌሎችን እንደ ረገምህ ልብህ ያውቃልና።
23እኔም ይህን ሁሉ በጥበብ ፈትኜ፣

“ጠቢብ ለመሆን ቈርጫለሁ” አልሁ፤
ይህ ግን ከእኔ የራቀ ነበር።
24ጥበብ ምንም ይሁን ምን፣
እጅግ ጥልቅና ሩቅ ነው፤
ማንስ ሊደርስበት ይችላል?
25ስለዚህ ጥበብንና የነገሮችን አሠራር ለመመርመርና ለማጥናት፣
የክፋትን መጥፎነት፣
የሞኝነትንም እብደት ለማስተዋል፣
አእምሮዬን መለስሁ።

26ልቧ ወጥመድ፣
እጆቿም እግር ብረት የሆኑ፣
አሽክላ የሆነች፣
ከሞት የከፋችዋን ሴት አገኘሁ፤
እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ከእጇ ያመልጣል፤
ኀጢአተኛውን ግን አጥምዳ ትይዘዋለች።
27ሰባኪው
ወይም የጉባኤ መሪ
እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ መርምሬ ያገኘሁት ነገር ይህ ነው፤

“የነገሮችን ብልኀት መርምሮ ለማግኘት፣
አንዱን በአንዱ ላይ በመጨመር፣
28ገና በመመርመር ላይ ሳለሁ፣
ግን ያላገኘሁት፣
ከሺሕ ወንዶች መካከል አንድ ቅን ሰው አገኘሁ፣
በእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ቅን ሴት አላገኘሁም።
29ይህን አንድ ነገር ብቻ አገኘሁ፤
እግዚአብሔር ሰውን ቅን አድርጎ መሥራቱን፣
ሰዎች ግን ውስብስብ ዘዴ ቀየሱ።”
Copyright information for AmhNASV